Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 391

12
March

‹‹ደጉ ሳምራዊ›› በኢትዮጵያ

Post by:

‹‹የኢትዮጵያውያን ችግር ችግሬ፣ እንባ እንባዬ፣ ጭንቀት ጭንቀቴ ሆኖ በትውልድ አገሬ ያሉትን፤ በማኅበራዊ ኑሮዋቸው የተጐዱ፣ በኢኮኖሚያቸው የደቀቁ ወገኖቼን መርዳት ግዴታዬ ነው፡፡

በቅዱስ መጽሐፍ እንደምናውቀው ‹ደጉ ሳምራዊ› ያለችኝን ሁለት ዲናርም ቢሆን ለወገኖቼ ባካፍል የተቸገሩት ወገኖቼ ችግራቸውን ያቃልላሉ፡፡ ለዚህም ስል ለ30 ዓመት ከኖርኩበት ጀርመን በመመላለስ ላለፉት 20 ዓመታት ወገኖቼን ስረዳ ቆይቻለሁ፡፡ ያለኝን ዕውቀትና አቅም በመጠቀምም ዕርዳታዬን እቀጥላለሁ፡፡››

ይህን ያሉት ላለፉት 20 ዓመታት ዋና መቀመጫውን በጀርመን ስቱትጋርት በማድረግና ካለፈው መጋቢት 2005 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ ቅርንጫፉን በአዲስ አበባ በመክፈት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የ‹‹ደጉ ሳምራዊ›› መሥራችና ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል መንገሻ ላለፉት 20 ዓመታት በ28 ሚሊዮን ብር የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማሳተፍ በትምህርቱ ዘርፍ ኢሉ አባቦራ፣ በሆሳዕና በባሌ፣ በቢሾፍቱ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎችም መዋለ ሕፃናትና የመጀመርያ ደረጃ  ትምህርት ቤቶች ሙሉ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት ያስገነቡ ሲሆን፣ በዱከም ያስገነቡት ሁለገብ የሆነ አዳራሽም ካበረከቷቸው ሥራዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ 

ሴቶች ረዥም ርቀት ተጉዘው ውኃ ከወንዝ ሲቀዱ፣ ዓለም በሠለጠነበት ዘመን እህል በእጃቸው ሲፈጩ፣ በማሽን እየታገዘ ሊሠራ የሚችል ሥራን በእጃቸው ሲሠሩ፣ ሲጐሳቆሉና አላግባብ ሲደክሙ ማየት ልብ ይሰብራል የሚሉት አቶ ዳንኤል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ራሳቸውን አግልለው ለሚኖሩት የፉጋ አካባቢ ነዋሪዎች ወፍጮ ቤት በመትከል፣ ውኃ ከጉድጓድ በመሳብ የንፁህ ውኃ ተጠቃሚ በማድረግ እንዲሁም በእጃቸው የሚሠሩትን ሸክላ በማሽን እየታገዙ እንዲሠሩ ቁሳቁሶችን ማሟላታቸውንና ገበያ እንዲያገኙ ማስቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ 

በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላና በደቡብ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት፣ ለነባር ሆስፒታሎች ቁሳቁስ በመለገስና እንዲሁም አዳዲስ በመገንባት፣ የታመሙና በየጐዳናው የተረሱ ወገኖችን በማሳከምና በማንሳት ያለፉትን 20 ዓመታት የዘለቁት አቶ ዳንኤል ለተማሪዎች የአገር ውስጥ ስኮላርሽፕ በማመቻቸትና በመስጠትም ይታወቃሉ፡፡ 

ኢትዮጵያውያን ቀጣይነት ካለው ልማት፣ ከተቀናጀ የጤናና የትምህርት እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ሲሠራ የቆየው ደጉ ሳምራዊ ቅርንጫፍ ቢሮውን አዲስ አበባ ከከፈተ ወዲህ ቀጣይ ልማቶችን በራሱ በኩል ለመተግበርና ከዚህ ቀደም ከነበረው ዕርዳታ በበለጠ ለተቸገሩት ለመድረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የደጉ ሳምራዊ በኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ጌታቸው ይናገራሉ፡፡

ዘላቂና የተቀናጀ ድጋፍ በማድረግ ከድህነት ነፃ የወጡና የተሻሻለ ኑሮ ያላቸው ኢትዮጵያውያንን ለማየት የሚሠራው ደጉ ሳምራዊ ከጀርመንና ከአሜሪካ መንግሥታት፣ ከጀርመናውያን ግለሰቦችና በጀርመን ከሚኖሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንደሚያገኝ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡

ፈረንጆች ብቻ መጥተው ኢትዮጵያን መርዳት የለባቸውም የሚሉት አቶ ዳንኤል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመቀናጀት በችግርና በጉዳት እንዲሁም መማር እየፈለጉ ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን በጋራም ይሁን በተናጠል እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡   

ባለፉት 20 ዓመታት በአጋሮቻቸው በኩል ካከናወኗቸው ተግባራት ከመንግሥት በኩል ቀና ትብብር የተደረገላቸው መሆኑንና ወደፊትም ትብብሩ ይቀጥላል ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት አቶ ዳንኤል በሙያቸው በጀርመን የኮሌጅ መምህር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ተጻፈ በምሕረት ሞገስ ፡ ምንጭ ሪፖርተር

Read 870 times